Psalms 33

ውዳሴ ለቸር አምላክ

1ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤
ቅኖች ሊወድሱት ይገባቸዋል።
2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፤
ዐሥር አውታር ባለውም በገና ዘምሩለት።
3አዲስ መዝሙር ዘምሩለት፤
በገናውን ባማረ ቅኝት ደርድሩ፤ እልልም በሉ።

4 የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነውና፤
የሚሠራውም ሁሉ የታመነ ነው።
5እርሱ ጽድቅንና ፍትሕን ይወድዳል፤
ምድርም በምሕረቱ የተሞላች ናት።

6 በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ተሠሩ፤
በአፉም እስትንፋስ የከዋክብት ሰራዊት።
7የባሕርን ውሃ በአንድ ዕቃ ይሰበስባል፤
ወይም የባሕርን ውሃ ይሰበስባል

ቀላዩንም በአንድ ስፍራ ያከማቻል።

8ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፤
በዓለም የሚኖር ሕዝብ ሁሉ በፊቱ ይንቀጥቀጥ።
9እርሱ ተናግሯልና ሆኑ፤
አዝዟልና ጸኑም።

10 እግዚአብሔር የሕዝቦችን ምክክር ከንቱ ያደርጋል፤
የሕዝብንም ዕቅድ ያጨናግፋል።
11 የእግዚአብሔር ሐሳብ ግን ለዘላለም ይጸናል፤
የልቡም ሐሳብ ለትውልድ ሁሉ ነው።

12 እግዚአብሔር አምላኩ የሆነው ሕዝብ፣
ለርስቱ የመረጠውም ወገን የተባረከ ነው።
13 እግዚአብሔር ከሰማይ ይመለከታል፤
የሰውንም ልጆች ሁሉ ያያል፤
14ከማደሪያው ቦታ ሆኖ፣
በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ይመለከታል፤
15እርሱ የሁሉን ልብ የሠራ፣
የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያስተውል ነው።

16ንጉሥ በሰራዊቱ ታላቅነት አይድንም፤
ጀግናም በኀይሉ ብርታት አያመልጥም።
17በፈረስ ድል አደርጋለሁ ማለት ከንቱ ተስፋ ነው፤
በብርቱ ጕልበቱም ማንንም አያድንም።
18እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች በሚፈሩት ላይ ናቸው፤
ምሕረቱንም በሚጠባበቁት ላይ አትኵረዋል።
19በዚህም ነፍሳቸውን ከሞት ያድናል፤
በራብ ዘመንም በሕይወት ያኖራቸዋል።

20ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤
እርሱ ረዳታችንና መጠጊያችን ነው።
21ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋል፤
በቅዱስ ስሙ ታምነናልና።
22 እግዚአብሔር ሆይ፤ ተስፋ ባደረግንህ፣
በእኛ ላይ ምሕረትህ ትሁን።
Copyright information for AmhNASV